Certificate of Registration of Access Real Estate Home Buyers Association

ይህ የአክሰስ ሪል እስቴት ቤት ገዢዎች ማህበር (አሪኤቤገማ) ድህረ ገጽ ነው። አሪኤቤገማ "ውለታው ይከበር!" በሚል መፈክር ሥር በተደራጁ ቤት ገዢዎች በሕጋዊ መንገድ የተመሠረተ ማኅበር ነው። ማኅበሩ በሲቪል ማሕበረሰቦች ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሠረት በ2013 ዓ.ም. ተቋቁሟል። ለአሪኤቤገማ መመሥረት ምክንያት የሆኑት ሁኔታዎች ከዚህ በታች በአጭሩ ተዘርዝረዋል።

የኢንተርኔት የውይይት ቡድናችንን ይቀላቀሉ

ከዚያ በኋላ የማኅበራችን አባል ይሁኑ

ቡድናችንን ለመቀላቀል ...

ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ አክሰስ ሪል ኤስቴት አክሲዮን ማኅበር አፓርትመንቶችን፣ ቪላዎችንና የንግድ ቦታዎችን በጣም ማራኪ በሆነ ዋጋ ለማቅረብ በገባው ቃል መሠረት ብዙዎች እየጎረፉ ቤት ገዙ። ቤት የገዛው ሰው ቁጥር አሁን አከራካሪ ቢሆንም የአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ ቤት የገዙት ቁጥር 2050 መሆኑን ከነዚህም ውስጥ 500 ያህሉ ስምምነታቸውን ሰርዘው ገንዘባቸውን ተመላሽ ማስደረጋቸውን ይጠቅሳሉ። ሌሎች ደግሞ የቤት ገዢዎች ብዛት 2,500 ነው ይላሉ። ትክክለኛው ቁጥሩ ምንም ይሁን ምን፣ ከቤት ገዢዎች በጠቅላላው 1.3 ቢሊዮን ብር የተሰበሰበ መሆኑን ይነገራል።

አክሰስ ሪል ኤስቴት በብር 50,000 መነሻ ካፒታል የተቋቋመ መሆኑን ይነገራል። ብዙም ሳይቆይ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማጠራቀም ቻለ። ቢበዛ 18 ወርና ቢያንስ በአንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የአፓርታማ ቤቶችን፣ ቪላዎችንና የንግድ ቦታዎችን ሠርቶ እንደሚያስረክብ የሚገልጹ አንፀባራቂ ብሮሹሮችን በማዘጋጀት ማስተዋወቅ ያዘ። በስምምነቱ መሠረት በተባለው ጊዜ ባያስረክብ ለዘገየበት ለያንዳንዱ ወር 5,000 ብር ለመክፈልም ግዴታ ገብቷል። የቤት ገዢዎች ስምምነታቸውን ቢሰርዙ ገንዘባቸውን እና 15% ወለድ እንደሚከፈል ዋስትና ተሰጥቷቸዋል።

እነዚህ ሁሉ አጓጊ ሁኔታዎች የብዙ ሰው ፍላጎት ሳቡና ብዙዎችን በብዙ ጥረት ያገኙትን ገንዘብ እንዲከፈሉ አድርጓቸዋል። ብዙዎች በማራኪ ቤቶችና አከባቢዎች ለመኖር ባላቸው ፍላጎት የተነሳ አንዳንዶቹ በሕይወት ዘመናቸው ቆጥበው ያጠራቀሙትን፣ ሌሎች ደግሞ መጦሪያቸውን ከፍለው ቤቶቹን ገዝተዋል።

እስከ 2006 ድረስ የቤት ገዢዎች ቤታቸው ሊደርስላቸው ይችላል ብለው በትዕግስት እየጠበቁ ነበር። ነገር ግን የአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ “ከሀገር እንደ ተሰደዱ” ሲያውቁ ትልቅ ግርግርና ቁጣ ተፈጠረ። ብዙ የፍርድ ቤት ጉዳዮች ተጀምረዋል። በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ትዕዛዝ፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ያካተተ አብይ ኮሚቴ ሰኔ 2016 ዓ.ም. የተመሠረተ ሲሆን የቴክኒክ ኮሚቴም ተቋቁሞ ነበር። እንደ አለመታደል ሆኖ እነዚህ ሁለት ኮሚቴዎች ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ አላመጡም።

"ዓብይ" ኮሚቴው ቤት ገዥዎች በማኅበር እንዲደራጁና "ከለሙትም ይሁን ካልለሙት መሬቶች" የቤት መሥሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው የሚል ሐሳብ ማቅረቡ ታውቋል። ይህ ሃሳብ ተግባራዊ ከሆነ የቤት ገዢዎች ከአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማህበር ጋር በገቡት ስምምነት የተቀመጡትን ዋና ቦታዎች እንደማያገኙ ግልጽ ነው። በተጨማሪም በቅድሚያ ሙሉ በሙሉ የከፈሉ ቤት ገዢዎች ደግሞ በራሳቸው ቤት ለመገንባት እንደገና መክፈል አለባቸው ማለት ነው።

የቤት ገዥዎች ኮሚቴው ከላይ የተጠቀሰውን ሀሳብ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሯሯጠ የነበረ ሲሆን ቤት ገዥዎችን ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ ሳያማክር በራሳቸው አቅም ቤታቸውን ለመሥራት እንደተስማሙ አድርጎ ሲያትት ቆይቷል። ይህ ደግሞ ለሁሉም እንኳ ባይሆን ለአብዛኛዎቹ የቤት ገዢዎች በጣም ተቀባይነት የሌለው ነው። ብዙዎች ከአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማህበር ለገዙት ግዢ ሙሉ በሙሉ ከፍለዋል። እንደገና እንዲከፍሉ መጠበቅ ፍጹም ኢፍትሐዊ፣ ምክንያታዊ ያልሆነና በማንኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው ነው።

ስለዚህ ይህ ሁኔታ አንዳንድ የቤት ገዢዎችን ጥቅሞቻቸው መጫወቻ አየሆኑ እያዩ ቁጭ ብለው ላለማየት አስገድዷቸዋል። ተሰባስበውም ከአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ጋር የገቡት ስምምነት እንዲከበርላቸውና ምንም ተጨማሪ ክፍያ የመክፈል ግዳታ ሳይጠበቅባቸው ቤቶቻቸውን እንዲያገኙ ለመጠየቅ ተገደዋል።

ችግሩ የተደራረበና በጣም ብዙ ነው። ከችግሩ በስተጀርባ በጣም ብዙ የግል ፍላጎት ያላቸው አካላት አሉ። ጉዳዩ ለአንዱ ብቻ ከተተወ የጥቅም ግጭት የሚፈጥር ነው። ስለዚህ፣ የቤት ገዢዎች ይህንን አሳዛኝ ጉዳይ በተሳካ ሁኔታ ለመጨረስ በአንድነት መተባበር አለባቸው።

ውለታው ይከበር!