የሥራ እርምጃ ማስታወቂያ - ከአክሰስ ሪል ኤስቴት ቤት ገዢዎች ማኅበር
17 Dec 2022 - የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ
ውድ የአሬህባ የውይይት መድረክ አባላት፣
የከበረ ሰላምታ እያቀረብን፣
የአክሰስ ሪል እስቴት ቤት ገዢዎች ማህበር (አሬህባ) በቅርቡ የአክሰስ ሪል እስቴት ድርሻ ኩባንያ ቦርድን ለማንቀሳቀስ ስለተደረገው ጥረትና ስለተገኘው ውጤት ቤት ገዢዎች ማሳወቅ ይፈልጋል። ሁላችሁም እንደምታውቁት አሮጌው የአክሰስ ሪል እስቴት ድርሻ ኩባንያ ቦርድ የቤት ገዢዎችን ለኪሳራ ከዳረገ በኋላ ለበርካታ ዓመታት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ሳያደርግ ቆይቷል። እስካሁን የአሬህባ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አሮጌውን የአክሰስ ሪል እስቴት ድርሻ ኩባንያ ቦርድ፣ የአቶ አክሎግን ቡድን፣ እንዲሁም አቶ ኤርሚያስ አመልጋን በአጠቃላይ ሁሉንም ወገኖች ለማሳተፍ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ጥረት ቢደረግም መፍትሄ ለማግኘት ከጎናችን ለመቆም ፈቃደኛ መሆናቸውን ያሳዮት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ብቻ ናቸው። የአሬህባ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አሮጌውን የአክሰስ ሪል እስቴት ኩባንያ ቦርድን (ወደ ቢሮአቸው በመሄድና ደብዳቤ በመጻፍ) ለመቅረብና ለመወያየት ጥረት ቢያደርግም ቦርዱ ለእኛ የቤት ገዢዎች ማኅበር እውቅና ለመስጠት ፈቃደኛ ሆኖ አልተገኘም ። አሁንም ድረስ የቤት ገዢ ተወካይ ነኝ ከሚሉት ከአቶ አክሎግም ተመሳሳይ ምላሽ ተሰጥቶናል።
የአሬህባ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በቀጣይ የወሰደው እርምጃም የድርሻ ኩባንያዎችን በበላይነት የመቆጣጠር ኃላፊነት ወደተጣለበት የመንግስት አካል ወደሆነው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርን መቅረብ ነበር። በዚህም መሰረት የሚከተለው ውጤትና ሂደት ላይ ተደርሷል ።
- አሬህባ ባደረገው ከፍተኛ ጥረት ከ10 በመቶ ያላነሰ ድርሻ ያላቸው የአክሰስ ሪል እስቴት ኩባንያ (ARE SC) ባለድርሻዎችን ፊርማ በማሰባሰብ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የባለድርሻ አካላትን ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራና አዲስ ቦርድ እንዲመርጥ አቤቱታአቸውን አቅርበዋል።
- በባለድርሻ አካላት በቀረበው አቤቱታ መሰረት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በፈረንጆች አቆጣጠር ኅዳር 30 ቀን 2022 የአሮጌው ቦርድ አባላትን እንዲሁም አቤቱታ አቅራቢ ባለድርሻዎችን ያካተተ ስብሰባ የጠራ ሲሆን በዚህ ስብሰባ ላይ አቶ አክሎግ እንደተገኙ ተዘግቧል። በስብሰባውም ላይ በአንድ በኩል አቤቱታውን በፈረሙት ባለድርሻ አካላትና በሌላ በኩል ደግሞ በአሮጌው ቦርድ ሁለት አባላት መካከል (በአቶ አክሎግ ተደራቢነት) ሞቅ ያለ ክርክር መደረጉን ሰምተናል።
- በስብሰባው መደምደሚያ ላይም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ትክክለኛውን አሰራር እንደሚከተልና "ሁሉንም የአክሰስ ሪል እስቴት ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ስብሰባ" በቅርቡ እንደሚጠራ ለሁሉም ተሳታፊዎች አሳውቋል።
- የአሬህባ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ስብሰባ ላይ የተካሄደው ክርክር ከመቼውም ጊዜ በላይ የአሬህባ አባላት አንድ ሆነው መቆም እንደሚያስፈልጋቸው የሚያመላክት መሆኑንና በዚህ የውይይት መድረክ ብቻ ላይ የምትገኙ ቤት ገዢዎች ማህበሩን መቀላቀል ወሳኝ መሆኑን ማስገንዘብ ይፈልጋል።
- በተጨማሪም የአሬህባ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በአሁኑ ጊዜ የአክሎግ ቡድን አንዳንድ የቤት ገዢዎችን ወደተሳሳተ አቅጣጫ ለመምራት እየሞከረ እንዳለ፣ እንዲሁም "ሁሉንም የአክሰስ ሪል እስቴት ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ስብሰባ" ፈጽሞ እንዳይጠራ አዲስ ቦርድም እንዳይቋቋም ጥረት እያደረገ መሆኑን ያውቃል። ከዚህ ጋር በተያያዘም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ትክክለኛውን ነገር እያደረገ እንዳልሆነ በመግለጽ የቤት ገዢዎችን ለማሳመንና የሚጠበቀው አዲስ ቦርድ እንዳይቋቋም ጥረት እያደረገ ነው። አሁን ያለውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርን እርምጃ ተከትሎ የቤት ገዢዎች ተስፋ ባደረጉበት በዚህ ወቅትና እነዚህ ሁሉ ዓመታት ካለፉ በኋላ "የአክሰስ ሪል እስቴት ባለድርሻን ንብረቶች እንደተጠበቁ አቆይለቻለሁ" በሚል ደካማ ምክንያት ንብረቶችን ለሚቋቋመው አዲስ ቦርድ አሳልፈው መስጠት እንደማይፈልጉ በማሳመን ሰበብ እስካአሁን የተደከመበትን ጥረት ከንቱ ለማረድረግ እየጣሩ ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት ተቃዋሚ እንቅስቃሴ ይጠበቅ የነበር በመሆኑ የአሬህባ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መፍትሄው ቤት ገዢዎች አብረው በመቆም ትግሉን መቀጠል መሆኑን ማስገንዘብ ይፈልጋል።
- የአክሰስ ሪል እስቴት ቤት ገዢዎች ማህበር (አሬህባ) አባል ያልሆናችሁ ይሁን እንጂ በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ብቻ ያላችሁ የቤት ገዢዎች "ተመልካች" መሆንን ትታችሁ አሁንም አሬህባን እንድትቀላቀሉ እንመክራለን። ሁላችንም ንብረታችንን ያጣን የቤት ገዢዎች እስከሆንን ድረስ "ተመልካች" መሆን ከእንግዲህ ትርጉም የለውም።
- አሬህባ በአሁኑ ጊዜ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሚወሰደውን ቀጣይ እርምጃ በቅርበት እየተከታተለ ይገኛል ። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም የአክሰስ ሪል እስቴት ኩባንያን (ARE SC) ለማስተዳደር አዲስ ቦርድ ምርጫን እንደሚያኬድ በማወቃችን ደስተኞች ነን።
- በመጨረሻም፣ በአሁኑ ጊዜ ከቤት ገዢዎች መካከል የአክሰስ ሪል እስቴት ኩባንያ (ARE SC) ባለድርሻ የሆኑትን ለይተን ለማወቅ እየጣርን መሆኑን ለቤት ገዢዎች ማሳወቅ እንፈልጋለን። ለሚኒስቴሩ የቀረበውን አቤቱታ ከፈረሙት ባለድርሻ አካላት መካከል የቤት ገዢ የሆኑ ለጊዜው ስለሌሉ ባለድርሻ የሆኑ ቤት ገዢዎች ማወቅ ለእኛ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህም የአክሰስ ሪል እስቴት ቤት ገዢዎች ማህበር የቤት ገዢ የሆኑ ባለድርሻ አካላት አዲስ በሚመሰረተው የአክሰስ ሪል እስቴት ኩባንያ (ARE SC) ቦርድ ላይ እዲወክሉን ለማድረግ ያስችላል ። በዚህም ጥረት የሁሉ ቤት ገዢዎች አስተዋጽኦ ያስፈልገናል፣ ስለሆነም የቤት ገዢ ከሆናችሁ ወይም ድርሻ ያለው የቤት ገዢ የምታውቁ ከሆነ በፍጥነት እንድታሳውቁን እንጠይቃለን ።
ከሰላምታ ጋር
የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፣ አሬህባ
ሌሎች ዘገባዎች በ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ
- የሥራ እርምጃ ማስታወቂያ - ከአክሰስ ሪል ኤስቴት ቤት ገዢዎች ማኅበር