የአክሰስ ሪል ኤስቴት ቤት ገዢዎች ማኅበር ተቋቁሞ የምዝበባ ምስክር ወረቀቱን ጥቅምት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ተረክቧል።
አክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማህበር ከቤት ገዥዎች ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት የገባውን ቃል ሳይፈጽም ሲቀርና የኩባንያው ሥራ አስኬያጅ ከአገር ከወጡ በኋላ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሰጡት ትዕዛዝ መሠረት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ያካተተ “አብይ ኮሚቴ" ተቋቁሟል። ይህ ኮሚቴ ችግሩን በማጥናት ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ የመፍትሄ ሃሳቦችን የማቅረብ ኃላፊነት ተሰጥቶ ነበር። ይሁን እንጂ ኮሚቴው ከቤት ገዢዎች ጋር አንድ ጊዜ ስብሰባ አድርጎ ኩባንያው እንዳልከሰረ ካረጋገጠ በኋላ ሌላ ስብሰባ ለማድረግ ለቤት ገዥዎች የገባውን ቃል ሳያከብር እራሱን እንዳፈረሰ አንዳንድ የቤት ገዢዎች ተረዱ።
ከዚያም ከቤት ገዢዎች ተወካዮች ኮሚቴ መካከል አንዳንዶቹ ራሳቸውን “አብይ ኮሚቴ" ብለው ከፈረጁ በኋላ በመንግስት የተቋቋመው ከፍተኛ ኮሚቴ ሥራውን ጨርሶ መፍረሱን ላልጠረጠሩ ቤት ገዥዎ ኮሚቴው ያለ በማስመሰል ውዥንብር መፍጠር ጀመሩ። በቀጣይም ቤት ገዥዎች በራሳቸው ቤት ለመገንባት ተስማምተዋል እና መሬቱ እንዲሰጣቸው በማለት መንቀሳቀስ ጀመሩ። እውነታው ግን የቤት ገዢዎችን ሰብስቦ መሬቱ ይሰጠንና ቤታችንን ራሳችን እንሠራለን ማለት አለማለታቸውን የጠየቃቸው ወገን አልነበረም።
የቤት ገዢዎች ተወካዮች ኮሚቴ የሁሉንም ቤት ገዢዎች ጥቅም ያስጠብቃል ተብሎ ይጠበቅ ነበር። ነገር ግን ኋላ ላይ ግልፅ እየሆነ እንደመጣው ከቤት ገዢዎች ጥቅም ጋር ተፃራሪ የሆነ ነገር በማራመድ ላይ መሆኑ ታወቀ። ይህንን ተከትሎም እራሱን “እውነተኞች ቤት ገዢዎች" እያለ የሚጠራው የቤት ገዢዎች ቡድን ብቅ አለ። ይህ ቡድን ራሱን “አብይ ኮሚቴ" እያለ የሚጠራውን ቡድን እንቅስቃሴ በመቃወም እንዲሁም የመልዕክት መላኪያ ዝርዝሮችን ፈጥሮም የቤት ገዢዎችን ማነጋገር ጀመረ።
በመጀመሪያ ከ1,500 በላይ የቤት ገዢዎችን በኢሜይል መልዕክት በኩል ለማነጋገር የተሞከረ ቢሆንም ትክክለኛ ወይም ተመራጭ መንገድ አልነበረም። ስለዚህ፣ የኢንተርኔት ቡድን በመፍጠርና ሁሉም የታወቁ የኢሜል አድራሻዎች ያላቸው የቤት ገዢዎች የኢንተርኔት ቡድኑን እንዲቀላቀሉ ግብዣ ተላከ። ለመጀመሪያው ግብዣ ምላሽ ላልሰጡ ቤት ገዢዎች ሌላ ሁለት ተጨማሪ ግብዣ ተልኳል። በዚህ መንገድ ይህ አዲስ ቡድን “አብይ ኮሚቴ” እየተባለ የሚጠራው ኮሚቴ በቤት ገዢዎች ላይ የጫነውን የመረጃ ሞኖፖሊ አፍርሷል። አሁን፣ የቤት ገዢዎች፣ የትም ሀገር ቢኖሩ፣ ከሌሎች የቤት ገዢዎች ጋር ሃሳብ መለዋወጥ ይችላሉ።
የቤት ገዢዎች ኢንተርኔት ቡድኑ የቤት ገዢዎች ብዙ ጥሩ ሃሳቦችን እንዲለዋወጡ ያስቻለ ቢሆንም ችግሩ ጥሩ፡ ጥሩ ሃሳቦችን ተከታትሎ መሬት ላይ ወርደው ወደ ተግባር እንዲገቡ የሚያደርግ አካል ያለመኖሩ ነበር። ስለዚህ አንዳንድ የቤት ገዢዎች “ማህበር” እንዲቋቋም ባቀረቡት ሃሳብ መሠረት የአክሰስ ሪል ኤስቴት ቤት ገዢዎች ማኅበር ሊቋቋም ችሏል።
የአሪኤገማ ዋና ተግባራት የሚከተሉት ናቸው።
ከላይ በቀረበው ሃሳብ መሠረት 43 የቤት ገዢዎች የማህበሩ መሥራቾች ሆነው ለመሥራት ፈቃደኛ ሆነዋል። ከነዚህ መካከል በአዲስ አበባም ሆነ በውጪ የሚኖሩ የቤት ገዢዎች ይገኙበታል። እነዚህ ቤት ገዢዎች በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ፎርም እንዲሞሉ እንዲሁም መታወቂያ፣ ፓስፖርት፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ ወዘተ. የመሳሰሉትን የመታወቂያ ሰነዶችን እንዲያቀርቡ ይጠበቅባቸው ነበር። ነገር ግን፣ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ 26 የቤት ገዢዎች ብቻ ሁሉንም መስፈርቶች በማሟላት ፊርማቸውን በመሥራችነት ማስቀመጥ ችለዋል።
በቀጣይም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ የተካሄደ ሲሆን የማኅበሩ የሥራ ሃላፊዎችም ስለራሳቸው ለሲቪል ማህበራት ድርጅት ባለሥልጣን ዝርዝር መረጃ እንዲሰጡ ተደርጓል።
ከዚያም የቢሮ ቦታ ተከራየን፤ በተጨማሪም አንዳንድ አባሎቻችን በበጎ ፈቃደኝነት ገንዘብ በመሰብሰብ ለቢሮአችን አገልግሎት የሚውሉ ሁለት ላፕቶፖችን ገዝተዋል።
በመጀመርያ በሥራ ዲሬክተርነት የሚያገለግል ተገቢው ብቃት ያለው አንድ ሰው ተገኝቶ የነበረ ቢሆንም የጠየቀው ክፍያ ከገንዘብ አቅማችን በላይ ስለነበር የነበረንን የገንዘብ አቅም ባገናዘበ ለመሥራት የተስማማ አንድ አመልካች ተቀጥሮ ለአራት ወራት ሠርቷል።
በአሁኑ ጊዜ ግን ሙሉ ጊዜውን የሚሰራ ዳይሬክተር የተቀጠረ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የቢሮ ረዳት የቀጠርነው የካቲት 2013 ውስጥ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የቢሮ ረዳት ቅጥር ቀጥሏል።
የቤት ገዢዎችን ለማግኘትና ወደ ቡድናችንና ማህበራችን እንዲቀላቀሉ ለማሳሰብ የተለያዩ መንገዶችን ሞክረናል። ቡድኑ የካቲት 2010 ዓ.ም. እንደተቋቋመ ከ1,500 በላይ ለሆኑ ቤት ገዢዎች ኢሜይል በመላክ የቡድናችን አባሎች እንዲሆኑ ጋብዘናል።
በኢሳት ቲቪ (በእያንዳንዱ ለአምስት ጊዜ የተደገመ የሁለት ዙር ማስታወቂያ)፣ በሸገር ኤፍ ኤም ራዲዮ በማስነገር የቤት ገዥዎች ወደ ቡድናችንና ማህበራችን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበናል። እንዲሁም አባሎቻችን ለሌሎች ላልሰሙ ቤት ገዢዎች እንዲነግሩ በማድረግ መረጃ እንዲደርሳቸው አድርገናል።
በጉዳዩ ያገባናል የሚሉ ወገኖችን ሁሉ በማነጋገር አብረውን እንዲሠሩ ስንጠይቅ ቆይተናል።
እንዲሁም ከቤታችን ጋር በተያያዘ ያሉብንን ችግሮች ለመፍታት ይረዳሉ ብለን የምናምንባቸውን ሁሉንም የመንግስት መሥሪያ ቤቶች አነጋግረናል፤ አሁንም እያነጋገርን እንገኛለን።