የማህበራችን የአክሰስ ሪል ኤስቴት ቤት ገዥዎች ማህበር አባል ለመሆን ፍላጎት ያለዎት በመሆኑ ደስተኞች ነን።

እንደሚገነዘቡት የማኅበር አባል መሆን ማለት በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብና በየጊዜው የማኅበሩ ጠቅላላ ጉባኤ በሚያስተላልፈው ውሳኔ መሠረት የመብትና የግዴታ ባለቤት መሆንን ያስከትላል።

አንድ ቤት ገዥ የማኅበራችን አባል ለመሆን አሁን ሥራ ላይ ባለው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ለመመዝገቢያ የአንድ ጊዜ ክፍያ 1,000.00 ብር ይከፍላል። በተጨማሪም ጠቅላላ ጉባኤው በሚወስነው መሠረት ወርኃዊ የአባልነት መዋጮ ያስከፍላል።

ከዚህ በታች ያለው ሊንክ (ማስፈንጠሪያ) አባል ለመሆን የሚያስፈልገውን መረጃ ይሰጥዎታል።

የማኅበራችን አባሎች ላልሆኑ የኢንተርኔት ቡድን አባላት

የኢንተርኔት ቡድን አባል ቢሆኑም እንኳ በቡድኑ በኩል የተደረጉት ውይይቶች ያልተከታተሉ ከሆኑ ብዙ ያመለጠዎት ነገር ሊኖር ይችላል። ስለዚህ በቅድሚያ የቡድኑ አባል ላልሆኑ ቤት ገዢዎች የተሰጠውን መረጃ ካነበቡ በኋላ ወደዚህ ተመልሰው ቢመጡ ይመረጣል።

የኢንተርኔት ቡድናችን አባል ከሆኑ የማኅበራችን አባል ለመሆን ማድረግ ያለብዎት ወደ

access_home_buyers@yahoo.com

ኢሜይል በመላክ የማህበራችን አባል ለመሆን እንደሚፈልጉ ማስታወቅ ነው። ከመልዕክትዎ ጋርም:-
  1. ከአክሰስ ሪል ኤስቴት አክሲዮን ማኅበር ጋር የተፈራረሙት ስምምነት የሁሉም ገጾች በጥሩ ሁኔታ የተሠራ ስካን ፎቶ ኮፒ፤

  2. ለገዙት ንብረት በሙሉም ይሁን በከፊል የከፈሉበት ደረሰኝ ስካን ፎቶ ኮፒ

በአባሪነት ይላኩልን።

መልዕክትዎ እንደደረሰን አስፈላጊው ተጨማሪ መረጃ እንልክልዎታለን።

የማኅበራችን አባል ለመሆን የሚፈልጉ ነገር ግን የኢንተርኔት ቡድን አባል ያልሆኑ ቤት ገዢዎች

የኢንተርኔት ቡድናችን አባል ካልሆኑ በቅድሚያ የኢንተርኔት ቡድኑ አባል ሆነው እንዲመዘገቡ ያስፈልጋል። ይህ የምንልበት ምክንያት፡-

  1. በሚደረጉት ውይይቶች ለመሳተፍ እንዲችሉ። የሚሰጡት ሐሳብ ባይኖርዎት እንኳ ሌሎች ቤት ገዢዎች የሚሉትን ለመከታተል ያስችልዎታል።

  2. ብዙ ቤት ገዢዎች ውጭ አገራት ስለሚኖሩ በቀላሉ ለመገናኘት ያስችላል።

  3. ወቅታዊ መረጃዎች ለመለዋወጥ ያስችላል።

  4. በተለይ ከማኅበሩ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጋር የሚደረገው ግንኙነት የወረቀት ሥራን በማስቀረት ወጪ ለመቆጠብ ያስችላል።

የኢንተርኔት ውይይት ቡድንና ማኅበር ለምን ማቋቋም እንዳስፈለገ በበለጠ ለማወቅ እንዲረዳዎ እባክዎ ቀጥሎ ያለውን ያንብቡ።

አሁን የምንገኝበትን ደረጃ ከመድረሳችን በፊት ሂደቱን የጀመረው "እውነተኞቹ ቤት ገዢዎች" የተባለ ቡድን ነበር። የአክሰስ ሪል ኤስቴት መፍረክረክ ሲጀመር በቤት ገዢዎች ዘንድ ብዙ ግራ መጋባት ተፈጠረ። በኋላ፣ "እውነተኞቹ የቤት ገዢዎች ቡድን" ብሎ ራሱን የሚጠራ ቡድን ተፈጠረ። ሁሉንም የቤት ገዢዎችን አንድ ላይ ለማምጣት ይህ "እውነተኞች የቤት ገዢዎች" ቡድን ኢሜይሎችን መላክ ጀመረ። በአንድ ኢሜይል ላይ ከ400 አድራሻዎች በላይ ማስፈር ስለማይቻል ሁሉንም ቤት ገዢዎች ለማዳረስ አንድ መልዕክት ለመላክ እያንዳንዳቸው እስከ 400 አድራሻዎችን የያዙ አምስት የኢሜይል መልዕክቶች መላክ ያስፈልግ ነበር።

ሥራውን ለማቃለል በሚያስችል መንገድ ሁሉንም ቤት ገዢዎች ለመድረስ የሚያስችል መድረክ መጠቀም አስፈላጊ ነበር። በመሆኑም ጥር 2010 ዓ.ም. ውስጥ የኢንተርኔት የውይይት መድረክ የተፈጠረው ወደ 2000 የሚጠጉ ኢሜይሎች ውስጥ በድግግሞሽ ገብተው የነበሩ አድራሻዎች ካጸዳ በኋላ እና 1,528 የኢሜይል አድራሻዎች ሲቀሩ ነው። በኢንተርኔት ቡድን አማካኝነት ከንብረቶቻችን ጋር የተያያዙ ብዙ ጉዳዮችን ተወያይተናል። በጥቅምት 2013 ዓ.ም. የአክሰስ ሪል እስቴት ቤት ገዢዎች ማህበር ሕጋዊ ምዝገባ እንዲካሄድ ያደረገው ማኅበር መመስረትን ጨምሮ ብዙ ጥሩ ሀሳቦች ተነስተዋል። በአሁ ጊዜ የተመረጠ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴና ቢሮ አለን።

የኢንተርኔት የውይይት መድረክ ከፈጠርን በኋላ፣ ለሁሉም የኢሜይል አድራሻዎች የአክሰስ ሪል ኤስቴት ቤት ገዥዎች ቡድንን እንዲቀላቀሉ ግብዣ ልከናል። የመጀመሪያውን ግብዣ ላልተቀበሉት ሁለት ተጨማሪ ዙር ግብዣዎች ተልከዋል። አንዳንዶች ግብዣው ወደ የመልዕክት ሳጥናቸው የደረሰ ቢሆንም ግብዣውን አልተቀበሉም። አንዳንዶች ደግሞ ግብዣዎች ቢላኩላቸውም በተለያዩ ምክንያቶች አልደረሱዋቸውም፤ ለምሳሌም ቤት ገዢዎች ከአክሰስ ሪል ኤስቴት አክሲዮን ማኅበር ጋር ከተፈራረሙ በኋላ የኢሜይል አድራሻቸውን በመቀየራቸው፣ ወይም ደግሞ አድራሻቸው በተሳሳተ መንገድ በመጻፉ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ አድራሻቸው ከሊስቱ ሳይገባ በመቅረቱ ግብዣ ያልተላከላቸው ሊኖሩ ይቻላሉ።

"የእውነተኞች የቤት ገዢዎች" ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ ቤታችን እንድናገኝ ይደረግ፤፤ በማለት የቤት ገዢዎች ፊርማ የማሰባሰብ ተግባር ጀምረው የነበሩ ሲሆኑ "የኢንተርኔት" የውይይት ቡድኑ መቋቋም ለዚህ ተግባርም አጋዥ ሆኖ ተገኝቷል። ምንም እንኳን አዎንታዊ እርምጃ ተወስዶ እንደሆነ የሰማነው ነገር ባይኖርም አቤቱታው ለመንግሥት የቀረበው በ523 የቤት ገዢዎች ተፈርሞ ነው።

ከላይ እንደተጠቀሰው በኢንተርኔት የውይይት መድርኩ በኩል ብዙ ጠቃሚ ነገሮች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ነገር ግን በውይይት ነጥረው የወጡ ጠቃሚ ጉዳዮች መሬት ላይ ወርደው ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችል መንገድ ባለመኖሩ ተግባራዊ ሳይሆኑ ይቀሩ ነበር። ለዚህ ችግር መፍትሄ ሊሆን ይችላል ተብሎ የቤት ገዢዎች ማኅበሩ ሊቋቋም ችሏል። የማኅበሩ መኖር በጉዳያችን ላይ በቋሚነት ክትትል ለማድረግ አስችሎናል።

ስለዚህ እርስዎም የበኩልዎን አስተዋጽኦ ለማበርከት እንዲችሉ በቅድሚያ ወደ ኢንተርኔት የውይይት ቡድናች ይቀላቀሉ። በመቀጠል የማኅበራችን አባል እንዲሆኑ ግብዣ ይላክልዎታል። ወደ ኢንተርኔት የውይይት ቡድኑ ለመግባት ቀጥሎ ካሉት ሁለት መንገዶች አንዱን ይጠቀሙ።

  • ወደ ኢንተርኔት ቡድናችን የመረጃ መረብ በመሄድ ያመልክቱ። አድራሻው፡-

    https://accesshomebuyers.groups.io/g/main

    የሚል ነው። ገጹ ላይ ወደታች ትንሽ ወረድ ብሎ

    የሚለውን ቁልፍ ጠቅ ካደረጉ በኋላ ቀጥሎ በሚመጣው ገጽ ላይ ያለውን በመሙላት መልዕክት ይላኩ።

  • ወይም ደግሞ ወደ

    access_home_buyers@yahoo.com

    የሚለው የኢሜይል አድራሻችን መልዕክት በመላክ መጠየቅ ይችላሉ።

ቤት ገዢ መሆንዎን አውቀን በፍጥነት እንድናስተናግድዎት፡-

  1. ከአክሰስ ሪል ኤስቴት አክሲዮን ማኅበር ጋር የተፈራረሙት ውል ሁሉም ገጾች በጥሩ ሁኔታ የተሠራ ስካን ፎቶ ኮፒ፤

  2. ለገዙት ንብረት ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል የከፈሉበት ደረሰኝ ስካን ፎቶ ከፒ፤

ይላኩልን። ይህን ካላደረጉ ግን እነዚህን ሰነዶች አንዲልኩ መልዕክት ስንለዋወጥ ጊዜ ይባክናል።