የአክሰስ ሪል ኤስቴት ቤት ገዢዎች ማኅበር የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወቅታዊ መግለጫ

04 May 2022 - ፕሮፌሰር ጥላሁን ተካ ወልዴ

ውድ አባላት፣

ከአክሰስ ሪል ኤስቴት ቤት ገዢዎች ማኅበር (አሪኤቤገማ) ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሞቅ ያለ ሰላምታ ለሁላችሁም ይድረሳችሁ። ይህ መልዕክት አክሰስ ሪል ስቴትስን በተመለከተ ምን እየተደረገ እንዳለ ለማሳወቅ ነው። መልእክቱ ግልፅ ነው፤ ሁላችንም ንብረታችንን ለማግኘት አእምሮአችንን እና እጆቻችንን አንድ አድርገን እንስራ። ማንም አያደርግልንም፣ እኛ ማድረግ አለብን። ለዚሁ አላማ "ውለታው ይከበር" በሚል መሪ ቃል አሪኤቤገማ መደራጀቱን ለመግለፅ እንወዳለን። ንቁ አባል ይሁኑ እና ረጅሙን እርምጃ አብረን በመጓዝ ንብረቶቻችንን እናስመልስ። እባክዎን ከዚህ በታች ያለውን ጥቂጥ ደቂቃዎች መድበው ያንብቡ።

ከመልካም ምኞት ጋር፤

ጥላሁን ተካ

የአሪኤቤገማ ፕሬዝዳንት


ለተከበራችሁ የአክሰስ ሪል ኤስቴት ቤት ገዢዎች

ሚያዝያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም.

የአክሰስ ሪል ኤስቴት አክሲዮን ማኅበር ያለበት ሁኔታ በተመለ ከተ ከተለያዩ የግሩፑ አባሎች ጥያቄዎች ሲቀርቡ ቆይተዋል። ጉዳዩን በተመለከተ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚያበሳጩና የሚያደናግሩ ብዙ ነገሮች አሉ። ቢሆንም በሕግ እውቅና አግኝቶ የተመዘገበው የአክሰስ ሪል ኤስቴት ቤት ገዢዎች ማኅበር አባሎች ግን ተጨባጭ መፍትሄው ምን ሊሆን እንደሚገባው ለመረዳት በርትተው ሲሠሩ ቆይተዋል።

ማኅበራችን ጉዳዩን ከሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በንቃት ሲከታተል ቆይቷል። አያሌ ስብሰባዎች ተደርገዋል፤ ደብዳቤዎች ለተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ተጽፈዋል። ከጥቂት ጊዜ በፊት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአክሰስ ሪል ኤስቴት አክሲዮን ማኅበር የባለአክሲዮኖች ስብሰባ ሊጠራ ይገባል የሚለውን ጥያቄያችንን ተቀብሎ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ የባለአክሲዮኖች ስብሰባ እንዲጠራ ለአክሰስ ሪል ኤስቴት አክሲዮን ማኅበሩ ቦርድ ትዕዛዝ ሰጥቷል። የባለአክሲዮኖች ስብሰባ መጥራቱ ቤቶቻችንን ለማግኘት ከሚያስችሉ እርምጃዎች ዋናው ቢሆንም የአክሰስ ሪል ኤስቴት አክሲዮን ማኅበር ቦርድ ስብሰባውን እስካሁን ድረስ አልጠራም።

ይህን ተከትሎ እንደተነገረን ከሆነ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የባለአክሲዮኖች ስብሰባ እንዴት ባለ ሁኔታ መዘጋጀት እንዳለበት እያሰበበት መሆኑን ነው። ቤት ገዢዎች እንድታስተውሉት የሚገባው ድምፃችን ሊሰማና የአክሰስ ሪል ኤስቴት አክሲዮን ማኅበር ተገቢው ድርጅታዊ አቋም ተመሥርቶ ሊቀጥል የሚገባው አሁን መሆኑን ነው።

ማኅበራችን የሚመለከታቸው የተለያዩ አካሎችን (ማለትም ኤርሚያስ ፣ አክሎግ ፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ፣ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ፣ ዳያስፖራ ኤጄንሲ ፣ ወዘተ) ጨምሮ አስፈላጊ የመሰሉትን ስብሰባዎች እና ክትትሎች ሲያደርግ ቆይቷል። ተገቢው የመረጃ መለዋወጫ መንገድ ይኖር ዘንድ ማኅበራችን የአክሰስ ሪል ኤስቴት አክሲዮን ማኅበር አዲስ ቦርድ ተመርጦ ተገቢ ቦታው ላይ እንዲገኝ በጉጉት እየጠበቀ ይገኛል።

በዚህ ወቅት ለተሻለና ለተፋጠነ መፍትሄ መገኘት የጋራ ድምፃችን ለማሰማት እንድንችል ቤት ገዢዎች በሙሉ የአክሰስ ሪል ኤስቴት ቤት ገዢዎች ማኀበር አባሎች ሆነው እንዲመዘገቡ ጥሪያችንን እና ምክራችንን እናቀርባለን። ከማኅበራችን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወቅታዊ መረጃ ለማግኘት ማድረግ ያለባችሁ በአባልነት ለመመዝገብ ያላችሁን ፍላጎት በመግለጽ ኢሜይል መላክ ብቻ ነው።

የግሩፓችን አባሎች የሆናችሁ እና በተጨማሪም የአክሰስ ሪል ኤስቴት አክሲዮን ማኅበር ባለአክሲዮኖች የሆናችሁ ሁሉ፣ ቤቶቻችንን ማግኘታችን እውን እንዲሆን የአክሰስ ሪል ኤስቴት አክሲዮን ማኅበር የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ እንዲደረግ፣ መተግበር የሚችል አዲስ ቦርድ እንዲሰየም ፣ በአክሲዮን ማኅበሩ መነቃቃት እንዲፈጠር ያላችሁን የግንኙነት መስመሮች በመጠቀም ግፊት እንድታደርጉ እናሳስባለን።

ከመልካም ምኞት ጋር የአክሰስ ሪል ኤስቴት ቤት ገዢዎች ማኅበር የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

ሌሎች ዘገባዎች በ ፕሮፌሰር ጥላሁን ተካ ወልዴ


  • የአክሰስ ሪል ኤስቴት ቤት ገዢዎች ማኅበር የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወቅታዊ መግለጫ